በአጎራባች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል ዘላቂ ሰላም እና አብሮነትን ለማጠናከር ያለመ የውይይት መድረክ ተካሄደ --------------------------- ሰንበቴ:ጷጉሜ 02/2018 ዓ.ም(ጆሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
በጅሌ ጥሙጋ፣ ኤፍራታና ግድም፣ አጣዬ እና ሰንበቴ ከተማ አስተዳደሮች መካከል ዘላቂ ሰላም እና አብሮነትን የበለጠ ለማጠናከር የውይይት መድረክ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
በአጎራባች ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ ለማጽናትና የሚጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍትሄ ለመስጠት አላማ በማድረግ የተካሄደ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ወቅት በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት እና ማህበረሰቡ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን ተቀራርቦ በንግግር በመፍታት አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተመላክቷል።
የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ የሁላችንም የዕለት ተዕለት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በየጊዜው ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በጋራ በመስራት የህዝቦቻችንን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ አባፍሮ ተናግረዋል።
አክለውም በአጎራባች ማህበረሰቦች መካከል ያሉ የጋራ እሴቶች እና ታሪካዊ ትስስሮች በመጠቀም ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ጽንፈኛ አመለካከቶችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች በበኩላቸው ከሕዝቡ እና ከአመራር አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን እና የጋራ የሰላም ኮሚቴዎችን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ አባፍሮን ጨምሮ፣ የአገር የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች እንዲሁም የአጎራባች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ሥራ አስፈፃሚ አካላት ተሳትፈዋል።