ሴራ አባ ኦርማ
አንዱና የመጀመሪያው ሴረ አባ ኦርማ ክፍል ጀላ ተብሎ የሚታወቅ ነው፡፡ጀላ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ትልቅና ሰፊ አውራጎዳና እንደማለት ሲሆን ይህም ህጉ ተጽፎና ተሰንዶ የሚታይና የሚዳሰስ ባይሆንም ነገር ግን በእያንዳንዱ ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ ለዘመናት የኖረና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ትልቅ ስርዓት ነው፡፡
ሁለተኛው የሴራ አባ ኦርማ ክፍል "Buuda/Baasa" በመባል የሚታወቅ ስርዓት ሲሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ የተለያዩ የወንጀል ዓይነቶች ተከስተው ሲታዩ/ሲገኙ/ የሚዳኙበት ስርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ በአይነቱ ለየት ያለ ወንጀል ተከስቶ ሲገኝ ሽማግሌዎች ተሰባስበው በመገናኘት ቁጭ ብለው እስቲ ይባባላሉ፡፡
እስቲ የሚለው ቃል ትርጉም የተከሰተው ወንጀል ከዚህ ቀደም ታይቶና ተሰምቶ የሚታወቅ ነወይ በማለት መጠያየቅና የንግግራቸው መንደርደሪያ የሚያደርጉት ቃል ነው፡፡ በመጨረሻም የተከሰተው ወንጀል በአካባቢውም ይሁን በሌላ አካባቢ ተክስቶ የሚታወቅ ሆኖ ከተገኘ በተከሰተበትና ከዚህ በፊት በተዳኘበት አግባብ የሚዳኝና የሚፈፀም ይሆናል፡፡ ይህ አይነት ስርዓት ከላይ እንደተጠቀሰው ጀላ በመባል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሽማግሌዎቹ ቁጭ ብለው ሲመክሩ የተከሰተው ወንጀል በአካባቢው ተሰምቶና ታይቶም የማይታወቅ ከሆነ ይህ ወንጀል ቡደ/ባሰ/ በመባል ይጠራል፡፡ በሌላ አነጋገር ትንግርት/ተዓምራዊ ክስተት/የሚል ትርጓሜ ይሰጠናል፡፡ ለዚህም ወንጀል የሚሰጠው ውሳኔ ልክ እንደ ክስተቱ አዲስነት ውሳኔውም በአይነቱ ለየት ያለ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ወንጀሉ ታይቶ የማይታወቅ፣ተሰምቶ የማያውቅና በተፈጸመው ወንጀል በ3 የወንጀል ዓይነቶች የሚቀጣ ይሆናል ማለት ነው፡፡