በቅርብ አጋር የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የተጀመረው የማህበረሰብ ውይይት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ --------------------------------- ሰንበቴ:ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በቅርብ አጋር የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ጤናማ ማህበረሰባዊ ግንኙነትን ለመፍጠር የተጀመረው የማህበረሰብ ውይይት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ከ3አር-ፎር-ካኬ (3R-4-CACE) ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ባከናወናቸው ተግባራት በወረዳው በተመረጡ ቀበሌዎች ሰፊ የውይይት መድረኮች እየተካሄደ ይገኛል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው መርሃ ግብር፣ በሁሉም የሙከራ ቀበሌዎች የሚገኙ ተወያይ ቡድኖች ሰባተኛ (7ተኛ) የውይይት ክፍለ ጊዜያቸውን አካሂደዋል። የዚህ ፕሮግራም የሙከራ ትግበራ በሙጤፈጫ እና ባልጭ ቀበሌዎች ስር በሚገኙ አራት ጎጦች ውስጥ ተደራሽ መደረጉ ታውቋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ ማህበረሰቡ በግንኙነቶቹ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና በቅርብ አጋር የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመገንዘብ ራሱን እንዲከላከል ማብቃት መሆኑ ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት የውይይት መድረኮቹን ሂደት የተመለከቱ ሲሆን ፕሮግራሙ በተወያዮች ላይ አውንታዊ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የ3R-4-CACE ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰይድ አሊ በቦታው በመገኘት በሰጡት አስተያየት "በቀበሌዎቹ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የውይይት መድረክ ማህበረሰቡ የባህርይ ለውጥ እንዲያመጣና ከፍተኛ መሠረት እየጣለ ይገኛል" ብለዋል።
አቶ ሰይድ አያይዘውም ማህበረሰቡ በግንኙነቶቹ ዙሪያ ነፃ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ባህል ማዳበሩ ለቀጣዩ ሰላማዊ አብሮነት ዋስትና መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም አሰራሮችን በማጠናከር ፕሮግራሙን በሌሎች ቀበሌዎችም እንደሚሰፋ ተናግረዋል።
በማህበረሰብ ውይይት መድረኮች ላይ አዋቂ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ወጣት ወንዶች እና ሴቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 432 የተለያዮ የማህበረሰብ ኮፍሎች በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው የውይይት መድረኩ ስለ ጤናማ ማህበረሰባዊ ግንኙነት ያላቸውን ግንዛቤ በእጅጉ እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ ጫናዎችንና ችግሮችን በግልጽ ውይይት የማድረግ ባህል አለመኖሩን በመግለጽ አሁን ግን ህግና ስነ-ምግባርን የተከተለ ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ ግንዛቤ አግኝተናል ሲሉ ተሳታፊዎቹ አስተያየታቸውን ጨምረው ሰጥተዋል።
በቅርብ አጋር የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች በቤተሰብና በማህበረሰብ ሰላም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ በመሆናቸው መከላከልን መሰረት ያደረጉት ውይይቶች የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከወረዳው ሴቶች፣ህፃናት፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል ።