ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የምትገኘው በአብክመ በኦሮሞ አስተዳደር ዞን ውስጥ በሰሜን ከአርጡማ ፉርሲ፣ በደቡብ ቀወት ወረዳና ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር፣በምዕራብ ኤፍራታ ግድምና ቀወት ወረዳ እንዲሁም በምስራቅ የአፋር ክልል ወረዳዎች ሀደለኢላና ሰሙ ሮቢ የምትዋሰን ሲሆን ከሀገራችንና መዲናችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ በስተሰሜን 265 ኪ.ሜ እርቃ ወደ ደሴ በሚወስደው በትልቁ አውራ መንገድ ላይ የትገኛለች፡፡ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር በስተምስራቅ 765 ኪ.ሜ እርቃ የምትገኝ ሲሆን፣ ከዞኑ መቀመጫ ከተማ ከሆነችው ከሚሴ በስተደቡብ በዋናው የደሴ አድስ አበባ መንገድ ላይ 63 ኪ.ሜ ላይ ትገኛለች፡፡
የአየር ሁኔታና የመሬት አቀማመጥ
የወረዳዋ አየር ንብርት 97% የሚሆነው በቆላማነት የሚታወቅ ሲሆን 3% የሚሆነው ወይና ደጋ ነው፡፡ የአየር ሙቀቷም ዝቅተኛው 240c ሲሆን ከፍተኛው 330c ነው፡፡ የወረዳዋ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ከ2,000- 2,600 ሚ. ሊ. እንደሆነ የወረዳዋ የአየር ንብረት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዝናብ ወቅቶችም ክረምትና በልግ ሲሆን የክረምቱ ወቅት ከሰኔ እስከ መስከረም የሚቆይ ሲሆን የበልጉ ወቅት ከየካቲት እስከ ሚያዚያ የሚቆይ ይሆናል፡፡ የወረዳዋ የመሬት ከፍታ ከባህር ወለል በላይ ከ500-700 ሜ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የወረዳዋ የቆዳ ስፋት 88,256 ሄ/ር ሲሆን የመሬት አቀማመጧም 31,052 ሄ/ር የሚሆነው ተራራማና ዳገታማ ሲሆን 57,204 ሄ/ር የሚሆነው ሜዳማ ነው፡፡ ከዚህ የመሬት አቀማመጥ ውስጥ 12,000 ሄ/ር የሚሆነው ለእርሻ መሬት የሚያገለግል ሲሆን 25,280 ሄ/ር የሚሆነው በደን ተሸፍኖ ይገኛል፡፡
የህዝብ ብዛትና የአኗኗር ሁኔታ
የሀገሪቱ የ1997 ዓ/ም ስታስቲክሳዊ የህዝብ ቆጠራ ውጤት (Census) መሰረት በማድረግ አሁን ላይ የወረዳዋ ህዝብ ቁጥር 65,873 ወንድ 67,479 ሴት በድምሩ 133,352 እንደሚሆን የገመታል፡፡ ከዚህ የህዝብ ቁጥር ውስጥ 88% የሚሆነው ኑሮውን በግብርና የሚመራ ሲሆን 12% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማራ እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡