የሰንበቴ ገበያ ዘወትር እሁድ ቀን በሰንበቴ ከተማ የሚዉል ትልቅ ገበያ ነዉ፡፡ ከዛሬ 250 አመት በፊት በድጉጉሩ አካባቢ ነዋሪ የነበሩ ሃጂ ቡሽራ የሚባሉ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ የሆኑ ግለሰብ በአካባቢዉ ብ/ሰቦች መካከል ያለዉን ግጭት ለማስወገድ ይህ ከተማ ባለበት ቦታ ገበያ እዳቋቋሙ ይነገራል፡፡ የገበያዉ ቀንም በመጀመሪያ እሁድ እለት ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ገበያዋ ሰኞ እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰኞ የስራ ቀን ስለሆነ እንደገና በደርግ ዘመን እሁድ እንዲሆን ተደረገ፡፡
የሰንበቴ ገበያ የብዙ ብሄሮች ስብጥር በመሆኗ ልዩ የትያትር መድረክ ያደርጋታል፡የኦሮሞ፣ አማራ፣ የአፋርና የአርጎባ ብሄረሰቦች ከነባህላዊ አለባበሳቸዉና አጋጌጣቸዉ በገበያዉ ሲገናኙ ለጎብኝዎች እንደሙዝየም አስደናቂ ሆነዉ ይገኛሉ፡፡ ባህላቸዉን የሚያዉቅ ሰዉ ያለአንዳች ችግር ማን የየትኛዉ ብሄር አባል እንደሆነ መናገር ይችላል፡፡ ይህ ብቻ አይደልም ይህን ገበያ የትያትር መድረክ ያስመሰለዉ፣ በገበያዉ ላይ የተለያዩ ባህላዊ ጌጣጌጥና አልባሳት እንዲሁም የእደጥበብ ዉጤቶች በብዛት መታየታቸዉ ነዉ፡፡ የዉጭና የአገር ዉስጥ ቱሪስቶች እነዚህን ባህላዊ ጌጣጌጥና አልባሳትን ሲገዙ በስፋ ይታያሉ፡፡