በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጉዳት ለደረሰባቸው እና በመንደር ቁጠባ ቡድኖች ለተደራጁ ሴቶች 800 የእርባታ ፍየሎች ግዥ እና ርክክብ መደረጉ ተገለጸ -------------------------------- ሰንበቴ:ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ከ3R-4-CACEP Component 2 ጋር በመተባበር በተለያዩ ገጠር ቀበሌዎች ጉዳት ለደረሰባቸው እና በመንደር ቁጠባ ቡድኖች ለተደራጁ ሴቶች ሲያከናውነው የነበረውን 800 የእርባታ ፍየሎች ግዥ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ርክክብ መደረጉ ጽ/ቤቱ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በአጣዬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ100 ሴቶች በፍየል እና በግ እርባታ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ሰልጣኞችን በሰለጠኑበት ዘርፍ ወደ ተግባር ለማስገባት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የእርባታ ፍየሎችን ግዥ ሲያከናውን መቆየቱ ተመላክቷል።
በዚህም ከወረዳው ገንዘብ ጽ/ቤት፣ ከእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት፣ ከህዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽ/ቤት፣ ከሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ከአጣዬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተውጣጡ የእንስሳት ባለሙያዎች፣ የቀበሌ ሊቀመንበሮች እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ግልጸኝነቱን በጠበቀ መልኩ የግዥ ሂደቱን አጠናቆ ለተጠቃሚወች ርክክብ አድርጓል።
በዚህ መሰረት;-
➢በጎሮ ድሬ በዳና ቀበሌ የሚገኘው ቢፍቱ የሴቶች የመንደር ቁጠባ ቡድን 163 ፍየሎች፣
➢በጎዳ ቀበሌ የሚገኘው ነብሮ የሴቶች የመንደር ቁጠባ ቡድን 159 ፍየሎች
➢በዱላ ቀበሌ የሚገኘው አብዲ ቦሩ የሴቶች የመንደር ቁጠባ ቡድን 153 ፍየሎች፣
➢በያቱ መረር ቀበሌ የሚገኘው ጉደቱ የሴቶች የመንደር ቁጠባ ቡድን 154 ፍየሎች፣ እንዲሁም
➢በወረ ሌንጫ ቀበሌ የሚገኘው ሰላም የሴቶች የመንደር ቁጠባ ቡድን 171 ፍየሎች ተረክበዋል።
ለእያንዳንዱ ሴት በተመደበ 95,000 ብር በአጠቃላይ 800 ፍየሎች ተገዝተው ለተጠቃሚዎች በይፋ እንዲተላለፉ ተደርጓል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፋጡማ ሰይድ ርክክቡ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ባለፉት ጥቂት አመታት ሴቶች በኢኮኖሚ ረገድ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማስቻል በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ኃላፊዋ አያይዘውም በዚህ አመት ከ3R-4-CACEP Component 2 ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የተከናወነው የፍየል ግዥና ርክክብ ሴቶች ከጥገኝነት ወጥተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት በብቃት እንዲለውጡ ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም የተጀመሩትን የስራዎች ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
የ3R-4-CACE ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰይድ አሊ በበኩላቸው የፍየል ግዥው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፍጹም ግልጽነት በሰፈነበት እና የሴቶቹን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ በማካሄድ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የፕሮጀክቱ ድጋፍ ውጤታማነት ዘላቂ እንዲሆን እና ተጠቃሚዎች ከእርባታው የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣታቸውን ለማረጋገጥ ከባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የድጋፍና የክትትል ስራዎች ይከናወናል ብለዋል።
በመጨረሻም 3R-CACE Component 2 ፕሮጀክት ሴቶች በገቢ ማመንጫ ስራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ እና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በአጠቃላይ 9 ሚሊዮን 500,000 ሺህ ብር ወጭ ማድረጉ ታውቋል።