የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 እቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄደ ------------------------ ሰንበቴ:ጷጉሜ 02/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የመድረኩ መክፈቻ ንግግር የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አሚናት ሙሄ አድርገዋል።
የተቋሙ ቡድን መሪ አቶ ሰዶመን በቴ የም/ቤቱን የ2018 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም በጥንካሬና በድክመት በዝርዝር አቅርበዋል።
በሪፖርቱ መሰረት የግምገማ መድረኩን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አሚናት ሙሄ እና የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አሜ ጠያር በጋራ መርተዋል።
አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አሚናት ሙሄ በንግግራቸው ምክር ቤቱ ሕዝብን በመወከል፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን የመቆጣጠር መሠረታዊ ተልዕኮውን በብቃት ሊወጣ የሚችለው ጠንካራ የክትትልና የግምገማ ሥርዓት ሲዘረጋ ብቻ መሆኑን አንስተው በመሆኑም የሕዝብን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የም/ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አሜ ጠያር በበኩላቸው ምክር ቤቱ የሰላምና የልማት አጋር የመሆን አላማውን ከግብ ለማድረስ የቀበሌ አፈ-ጉባኤዎች ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጸው በየደረጃው ያሉ አካላት የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ በባለቤትነት ስሜት በመምራት የቁጥጥር እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙ የቀበሌ አፈ-ጉባኤዎች እና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች መኖራቸውን አንስተዋል።በመሆኑም በቀጣይ በ2019 ዓ.ም የምክር ቤቱን ተልዕኮና ራዕይ በሚመጥን መልኩ የህዝብ ተጠቃሚነትን ይበልጥ የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በ2018 ዓ.ም በስራ አፈፃፀማቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የቀበሌ አፈ-ጉባኤዎች፣ የወረዳ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም ለጽ/ቤቱ ባለሙያዎች እውቅና እና ማበረታቻ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።