ከሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጋር ውይይት ተካሄደ --------------------------- ሰንበቴ:ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ "ውጫዊ የወረራ ስጋት እና ውስጣዊ የፅንፈኝነት አደጋን በመቀልበስ ዘላቂ ሰላምና ልማትን እናረጋግጣለን!" በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞችን በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና መልካም አስተዳደር ዘርፎች በመመደብ መካሄዱ ተገልጿል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ መሀመድ እና የፓርቲው አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አሚናት አሊይ በመድረኮቹ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
አቶ አሊ መሀመድ በመክፈቻ ንግግራቸው የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ የውጫዊና ውስጣዊ ስጋቶችን ምንጭ በትክክል መረዳትና በጋራ መመከት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ወ/ሮ አሚናት አሊይ በበኩላቸው ህዝባዊ አንድነትን ማጠናከርና የሰላምና የልማት ጸር የሆነውን ፅንፈኝነትን በጋራ በመታገል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የሴክተር ሰራተኞች በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ ህዝቡን በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኡመር እና ግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ አብደላ ሙሣ የውይይቱን መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በቀረበው መነሻ ጽሁፍ ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝር ተዳሷል።በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ወጫዊ ስጋቶች እና በውስጥ በኩል የሚስተዋሉ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴዎች የሀገርን ህልውና እና የህዝቦችን አብሮነት የሚፈታተኑ መሆኑ ተመላክቷል።በመሆኑም እነዚህን አደጋዎች በጋራ በመቀልበስ ሀገራዊ ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባ ተገልጿል።
መነሻ ጽሁፉን መሰረት በማድረግ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ወቅታዊውን ሀገራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የወረራና የፅንፈኝነት ስጋቶችን ለመመከት እና የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ሀገሪቱ አሁን ካጋጠማት ውጫዊ ስጋት እና ውስጣዊ የፅንፈኝነት አደጋ ለመቀልበስ የሀገርን ህልውና የሚያስከብር ጠንካራ የመከላከል አቅምን መገንባት፣ ህዝባዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ውስጣዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ የፅንፈኞች ፕሮፖጋንዳ አስቀድሞ መገንዘብ እና መመከት እንዲሁም ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር ግንባር ቀደም መሆን እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ እና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ ተጠናቋል።