በአጎራባች ወረዳዎች መካከል “የሰላም እና የዳዕዋ ኮንፈረንስ” ተካሄደ ----------------------------- ሰንበቴ:መስከረም 09/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
በጅሌ ጥሙጋ እና ሀደለኤላ ወረዳዎች አዋሳኝ ቀበሌዎች መካከል ማህበራዊ ትስስር እና ሰላምን ለማጠናከር በአደሌሌላ ከተማ የሰላም እና የዳዕዋ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
የኮንፈረንሱ ዓላማ ለዘመናት በባህል፣ በሃይማኖት እና በማህበራዊ ጉዳዮች ተሳስረው የኖሩትን አጎራባች ማህበረሰቦች ሰላም እና ወንድማማችነት ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ አብሮነትን ለማዳበር እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም በአጎራባች ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ተቀራርቦ በመወያየት እና በመግባባት ለመፍታት መሆኑ ተመላክቷል።
በእለቱ ውይይት እና ዳዕዋ የተደረገ ሲሆን በሁለቱ ወረዳ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ መተማመን እና አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ግንዛቤ የተፈጠረ ሲሆን በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን የቆየ አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የጋራ ሰላምን ማጠናከር እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ይህ በእንዲህ እያለ ሰላምና አብሮነትን በመገንባት የአካባቢውን ሰላም ለማሰጋገጥ በሌሎች አዋሳኝ ቀበሌዎችም ተመሣሣይ የሰላም እና የዳዕዋ ኮንፈረንስ ይካሄዳል ተብሏል።
በመጨረሻም በመርሐ-ግብሩ የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሰይድ፣ የሀደለኤላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሎኬ፣ የቀድሞው የአፋር ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) ም/ፕሬዚዳንት ሸኽ ሙሳ መሐመድ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ዑለማዎች፣ የዳዕዋ አስተባባሪዎች፣ አባገዳዎች፣ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች መሣተፋቸው ታውቋል።