በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ አካሄደ።
መድረኩ ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል፣ ክፍተቶችን ለማረም እና የአዲሱን ትምህርት ዘመን ዝግጅት ለማቀላጠፍ ያለመ ነው።
በመድረኩ የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካቢር ሐሰን እና የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጀቤሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክትና የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
በመቀጠልም የትምህርት ጽ/ቤቱን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የትምህርት ሥርዓት ቡድን መሪ አቶ ጁሃር አህመድ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በሪፖርቱ ላይ በመነሳት ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የቀረበው የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የትምህርት ሥራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ የተስተዋሉ ችግሮችንና ክፍተቶችን በዝርዝር ያቀረበ ነበር።
በተለይም በ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል በ2018 ዓ.ም በተካሄዱ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡና የሚታይ ስኬት መገኘቱ በሪፖርቱ ተጠቁሟል። ይህም የወረዳው ትምህርት ዘርፍ በተማሪዎች ውጤት ላይ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን የሚያመላክት ሲሆን፣ 2018 ዓ.ም በትምህርት ዘርፉ የስኬት ዓመት መሆኑም ተገልጿል።
በውይይቱም በ2018 ዓ.ም የተገኙ ስኬቶችን የበለጠ ማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን በተገቢው ማረም፣ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እና በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎችን በተቀናጀና በውጤት ተኮር መንገድ ለመፈጸም የሚያስችሉ የሥራ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በተጨማሪም የ2019 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባን በስኬት ለማከናወን፣ ተማሪዎችን በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት ማስመዝገብ፣ ወላጆችና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የተማሪ ምዝገባን ማስፋት እና ተማሪዎች ያለ ትምህርት እንዳይቀሩ በቅንጅት መሥራት ላይ አተኩሮ ተሰጥቷል።
መድረኩ በ2018 ዓ.ም የተገኙ የትምህርት ስኬቶችን የበለጠ በማጠናከር፣ ከክፍተቶች በመማርና በ2019 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባን በተሻለ ደረጃ በማከናወን የትምህርት ሥርዓቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በተያዘ አቅጣጫ ተጠናቋል።