በአርባዋዮ ቀበሌ እየተከናወነ ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጎበኘ ---------------------------------- ሰንበቴ:ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን) የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እና የሰክተር የሥራ ሃላፊዎች በአርባዋዮ ቀበሌ በመገኘት በ3R-CACE ፕሮጀክት እየተገነባ የሚገኘውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴ በአካል በመዘዋወር ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም የፕሮጀክቱን የስራ አፈፃጸም እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመገምገም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በአርባዋዮ ቀበሌ ከ3,052 በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረው ፕሮጀክት በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም የህብረተሰቡን የውሃ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ወረዳ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
በእቅዱ መሰረት 200 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር የታቀደ ሲሆን አሁን ላይ 150 ሜትር ጥልቀት ላይ የውሃ ማጣራት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛል ተብሏል።
የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በሰከንድ ከ40 እስከ 50 ሊትር ውሃ የማስወጣት ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ይህም የቀበሌውን ነዋሪዎች የውሃ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሸፍን ተመላክቷል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ውሃና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ በቦታው በመገኘት በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የውሃ ችግር በመሰረታዊነት የሚፈታ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘውም አሁን ላይ የቁፋሮ እና የማጣራት ስራዎች በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሰይድ የፕሮጀክቱን የስራ እንቅሰቃሴ ከተመለከቱ ቡኃላ የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራዎች በአጭር ግዜ በማጠናቀቅ በቀጣይ የስርጭት መስመሮች ዝርጋታ እና የማጠራቀሚያ ታንከር ግንባታዎችን በማከናወን ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ አቅጣጫ ሰጥተዋል።